Tags » Ethiopians

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ቃሊቲ ተዛወረ

(ነገረ ኢትዮጵያ) በሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ ነህ ተብሎ የአስራ አራት አመት እስር የተፈረደበት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በእስር ከሚገኝበት የዝዋይ እስር ቤት ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ቃሊቲ ተዛወረ፡፡


የጋዜጠኛ ውብሸት ባለቤት ወ/ሮ ብርሃኔ ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለጸችው ውብሸት ከዝዋይ ወደ ቃሊቲ ከተዛወረ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ‹‹ሆኖም ግን ብዙ ሰዎች ውብሸት ወደ ቃሊቲ መዛወሩን መረጃው የላቸውም›› ያለችው ወ/ሮ ብርሃኔ፣ ‹‹አሁን ውብሸት ቃሊቲ በፊት ለፊት በር በኩል ዋይታ ቤት በሚባለው በኩል ይገኛል፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ ሙሉ ቀን ሊጠይቀው የፈቀደ ሁሉ መጠየቅ ይችላል›› ብላለች፡፡

ውብሸት ወደ ቃሊቲ የተዛወረበት ምክንያት የቤተሰብ ጉዳይ ስላለበት መሆኑን የጠቀሰችው ወ/ሮ ብርሃኔ ባለቤቷ ቃሊቲ የሚቆየው ላልተወሰነ ጊዜ መሆኑን ገልጻለች፡፡ ‹‹እስከ መቼ ቃሊቲ እንደሚቆይ ባላውቅም መስከረም 29 ቀጠሮ ስላለው እስከዚያው በዚሁ እንደሚቆይ እገምታለሁ›› ብላለች፡፡
ጋዜጠኛ ውብሸት የአንድ ልጅ አባት ሲሆን ቀደም ሲል ዝዋይ እስር ቤት እያለ ልጁን ለማየት ፈተና እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹አሁን ለጊዜውም ቢሆን ልጃችንን ይዠ ስለምጠይቀው ልጁን ቶሎ ቶሎ ማየት ችሏል›› ስትል ወ/ሮ ብርሃኔ ለነገረ ኢትዮጵያ ተናግራለች፡፡
የውብሸት ልጅ ፍትህ ውብሸት ይባላል፡፡ ይህ ህጻን ‹‹እኔም ሳድግ እንደ አባቴ እታሰራለሁ?›› ሲል መጠየቁ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በእስር ቤት ሆኖ የጻፈው ‹‹የነጻነት ድምጾች›› መጽሐፍ ለንባብ መብቃቱን ባለቤቱ ወ/ሮ ብርሃኔ ገልጻለች፡፡

Addis Ababa

የጊፍት ሪል ስቴት ባለቤት ታሰሩ

የጊፍት ሪል ስቴት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ዋና ሥራአስኪያጅ አቶ ገብረየሱስ ኢተጋ በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የሊዝ ቦርድ ከተፈቀደላቸው መሬት በላይ ይዘው በመገኘታቸው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

አቶ ገብረየሱስ በቀድሞ ወረዳ 28 ልዩ ስሙ የካ አባጣፎ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ ከተረከቡት መሬት በተጨማሪ ከ30ሺ ካሬሜትር በላይ ይዘው በመገኘታቸውና እንዲያስረክቡም በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሆነው ባለመገኘታቸው ከትላንት በስቲያ ሰኞ ዕለት በቁጥጥር ሥር ውለው ትላንት ፍ/ቤት መቅረባቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

ምንጮቻችን እንዳመለከቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሊዝ ቦርድ ለጊፍት ሪል ስቴት በቀድሞ ወረዳ 28 የካ ለገጣፎ አካባቢ የሚገኝ 13 ሄክታር መሬት ቦታ 21 ባለ 3 ፎቅ ኮንዶሚኒየም፣ 81 ቪላ ቤቶች፣ በመጀመሪያ ፌዝ ለመገንባት፣ 20 ኮንዶሚኒየም ሕንጻ እና 130 ቪላ ቤቶች መዝናኛ ሱቆችና ቢዝነስ ሴንተር ያለው ግንባታ በሁለተኛው ፌዝ ለመሥራት በሪል ስቴት መመሪያው መሠረት የሊዝ ዋጋውን ከፍሎ በሊዝ ቦርድ ቃለጉባዔ ቁጥር 4/97 በቀን 2/2/1997 እንዲወስዱ ተወስኗል። ሆኖም ጊፍት ሪል ስቴት የውል ማሻሻያ አድርገናል በማለት የመሬት መጠኑን አሳድጎ በሕገወጥ መንገድ ትርፍ መሬት መያዙን አስተዳደሩ አረጋግጧል። ይህንን ጉዳይ በቀድሞ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው አስተዳደር ጥቆማ ቀርቦለት የካቲት 17 ቀን 2004 ዓ.ም በቃለ ጉባዔ ቁጥር 18/2004 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ጊፍት ሪል ስቴት በሕገወጥ መንገድ የወሰደውን መሬት እንዲመልስ ወስኖ ክፍለ ከተማውም በእጁ የሚገኘውንም ካርታ እንዲያመክን ማዘዙን ምንጮቻችን አስታውሰዋል።

ጊፍት ሪል ስቴት በተደጋጋሚ ጉዳዩን አስመልክቶ ያቀረበው አቤቱታ አስተዳደሩ ሊቀበለው አልቻለም። በዚህ መሠረት በአቶ ድሪባ ኩማ የሚመራው አስተዳደር በ24/10/2006 በቁጥር አ.አ/ከጽ/03/7.7/390 በከንቲባ ጽ/ኃላፊ በአቶ አሰግድ ፊርማ በተፈረመ ደብዳቤ የሪልስቴቱ የአቤቱታ ጥያቄ ውድቅ መሆኑ ተገልጾለታል። ይህም ሆኖ ግን ጊፍት ሪል ስቴት ወደመሬት ባንክ እንዲገባ በተወሰነው ይዞታ ላይ ግንባታ በመጀመሩ የአስተዳደሩ ፍትህ ጽ/ቤት ከዓቃቤ ሕግ ጋር በመቀናጀት አቶ ገብረየሱስ ኢተጋ ሰኞ እለት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ከፍ/ቤት የመያዣ ትዕዛዝበማውጣት ግለሰቡን በቁጥጥር ስር በማድረግ ተባባሪዎችንም በመፈለግ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። አቶ ገብረየሱስ ትላንት በአዲስ አበባ ከተማ የካ ምድብ ችሎት ፍ/ቤት ቀርበው ፖሊስ ምርመራውን ለማጣራት የጠየቀውን የሰባት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ እንደተፈቀደለት ለማወቅ ተችሏል።

ጊፍት ሪል ስቴት በሕገወጥ መንገድ ይዞታል የተባለው ይዞታ በወቅቱ የመሬት ሊዝ ጨረታ ከፍተኛ ዋጋ ሲሰላ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ግምት እንዳለው ምንጫችን ጠቁሟል።

ምንጭ፡ ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ

Addis Ababa

ቴዲ አፍሮ ከ9 ዓመት በፊት ሆላንድ መድረክ ላይ የተጫወተው ዘፈን እንደአዲስ መለቀቁን “ሕጋዊነትን ያልተከተለ ስርጭት” አለው

  •  

(ዘ-ሐበሻ) ዛሬ በሶሻል ሚዲያዎች ከፍተኛ አድማጭን ያገኘውን “ቀስተዳመና” የተሰኘውን ነጠላ ዜማ በማሰመልከት ቴዲ አፍሮ በፌስቡክ ከገጹ በሰጠው ቃል “ሕጋዊነትን ያልተከተለ ስርጭት” ሲል አወገዘው።

አርቲስቱ በፌስቡክ ገጹ እንዳለው “ቀደም ሲል (ሰባ ደረጃ) በሚል ርዕስ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በኦፊሻል ድረ ገጱ ላይ አዲስ ሙዚቃ መልቀቁ ይታወቃል። ነገር ግን የዚህን ስራ መዉጣት ተከትሎ በቅርብ ጊዜ ዉስጥ ከአርቲስቱ እዉቅና ዉጪ በሶሻል ሚዲያዉ ላይ የተሰራጨ ሕጋዊነት የሌለውና ከዘጠኝ አመት በፊት አርቲስቱ በሆላንድ አገር መድረክ ላይ የተጫወተዉን ጥራቱን ወይም ደረጃዉን ያልጠበቀ ሙዚቃ ባልታወቁ ወገኖች እንዲሰራጭ ተደርጓል። ይህ እንዲሆን ያደረጉት ወገኞች ምክንያትም ሆነ ምንጭ ለጊዜዉ ባይታወቅም፡ ጉዳዩ ከአርቲስቱ የኮፒራይት መብት አንጻር ሲታይ ሕጋዊነትን ያልተከተለ በመሆኑ እዉቅና የሌለዉ ስርጭት መሆኑን ለአርቲስቱ አድናቂዎችና ወዳጆች በሙሉ ለመግለጽ እንወዳለን።”

Addis Ababa

በህወሀት እና በአጋር ፓርቲዎቹ መካከል አለመተማመን እየተፈጠረ ነው

እስከ ጳጉሜ 4 2006 ዓ.ም ድረስ የተካሄደው የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በርካታ እንግዳ ክስተቶችን ይዞ የተገኘ እንደነበር ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልጸዋል:: በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ለሶስተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚሁ የድርጅቱ ስብሰባ ብአዴን እና ኦህዴድ ድርጅታዊ ተልእኮዎችን የማስፈጸም ውስንነት እንደታየባቸው አልፎ ተርፎም የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች በተለይም ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ ኢሊባቡር እና አምቦ የኦነግ ምሽግ የሆኑ ሲሆን በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር በአርበኞች ግንባር ቁጥጥር ስር ለመዋል እንደተቃረበ፣ በአመራሩ እንዝህላልነት ህዝቡ ከኢህአዴግ እየራቀ እና ለድርጅቱ ጀርባውን እንደሰጠ ከመድረክ ተገልጽዋል:: በዚህ ጉዳይ ላይ የተናገሩት የብአዴን እና የኦህዴድ አመራሮች የተቀሰው አካባቢ ገብቶ ለመስራት ፍቃደኛ የሚሆኑ አባላት እጥረት እንዳለ፣ ህዝቡ በተደጋጋሚ በአካባቢው አመራሮች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደሚያደርስ ገልጸው ይህም ሊሆን የቻለው በአካባቢው ያለው የሀይል እጥረት እንደሆነ ገልጸዋል::

በሌላ በኩል በብኣዴን እና በኦህዴድ ውስጥ የሚገኙ አባላት ድርጅታዊ ታማኝነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እየመጣ እንደሆነ በርካታ አባላት በየሄዱበት ሀገር ጥገኝነት በመጠየቅ ላይ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን መጪው የ2007 ምርጫ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ሁሉም መሰረታዊ ድርጅቶች አባላታቸውን ጠንክረው እንዲያንቀሳቅሱ በተጨማሪም የሚዲያው ክፍል ልማታዊ አርቲስቶች ወደ ህዝቡ ልብ እንዲገቡ መሰራት እንዳለበት ለዚህም እቅድ ተነድፎ በቅርቡ ለሚዲያው ክፍል ገቢ እንደሚሆን እና ስራው ተግባራዊ እንደሚሆን ከመድረክ ተገልጹአል::

በሌላ በኩል ህወሀት በ2007 ቴዎድሮስ አድሀኖምን የድርጅቱ ኮከብ በማድረግ ላቅ ብሎ ለመታየት የሚያደርገው ሙከራ በአንዳንድ የኦህዴድ እና የብአዴን አባላት ተቃውሞ ሊያስነሳ እንደሚችል የተገመተ ሲሆን ከዚህ ሁሉ ነገር ጸድቶ ትክክለኛ የህወሀት ስራ አስፈጻሚ ሆኖ እየሰራ የሚገኘው ደህዴን እንድሆነ ለማወቅ ተችሉአል::

በተያያዘ ዜና ህወሀት እና የተቃዋሚው ቡድን ለእርቀ ሰላም ይቀመጡ ዘንድ በአፍቃሪ ህወሀቶች ዘንድ ውስጥ ውሰጡን ስራ እየተሰራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፣ ይህንንም ስራ በበላይነት ይዘው እየሰሩ ያሉት አቶ መነገሻ ስዩም እንደሆኑ በተጨማሪም አሜሪካን ሀገር ሜሪላንድ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ዶ/ር ጥላሁን በየነ በቡድኑ ውስጥ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችልዋል::

የእርቀ ሰላሙ ጉዳይ ከየትኛው ወገን እንደተነሳ ባይታወቅም የተለያዩ አስተያየት ሰጪ የኢህአዴግ አባላት ህዝቡ ከኢህአዴግ በተቃራኒ በመቆሙ በተለይም በሐገር ውስጥ በትግራይ ክልል የአረና ፓርቲ ተቀባይነት ማግኘት በመሀል ኢትዮጵያ ደግሞ የሰማያዊ እና የአንድነት ፓርቲዎች መጠናከር በሚጠሩት ሰልፍ ላይ የሚገኘው የህዝብ ቁጥረ ከእለት ወደ እለት መጨመር በውጪ ሀገራት ደገሞ ግንቦት ሰባት እና የአርበኞች ግንባር ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ወደ አንድ መስመር መምጣት በህወሀት ነባር አመራሮች ለድርጅታቸው እንደ አደጋ በመታየቱ የእርቀ ሰላሙ ጉዳይ ከህወሀት አመራሮች ሊነሳ እንደሚችል ይገመታል፣ በተቃዋሚው በኩል በእርቀ ሰላሙ ዙሪያ ያለው ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም።

Addis Ababa

በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ የተላለፈው መልዕክት ጽሑፍ

እንደምን አመሻችሁ!

በዚህች መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቤተሰቦቹና ከወዳጆቹ ጋር ሆኖ አዲሱን አመት ለመቀበል በሚዘጋጅባት ምሽት በግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ስም እንኳን ለአዲሱ አመት በሠላም አደረሳችሁ ስል ከፍተኛ ክብርና ትልቅ ደስታ ይሰማኛል። መቼም በባህላችን ለሠላም ያለን ቦታ ከፍተኛ ስለሆነ አዲስ አመት በመጣ ቁጥር እንኳን በሠላም አደረሳችሁ እንባባላለን እንጂ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሠላም ከጠፋ ብዙ አመታት ተቆጥረዋል።

Addis Ababa

ዶ/ር ዳኛቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሊከስሱ ነው

      በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ የዩኒቨርሲቲው የአመት ፍቃድ አሰጣጥን በተመለከተ የተፈጠረው አለመግባባት ሊፈታ ባለመቻሉ በመ/ቤታቸው ላይ ክስ ሊመሰርቱ እንደሆነ ተናገሩ፡፡
በዩኒቨርስቲው ህጋዊ አሠራር መሰረት 6 አመት ያስተማረ አንድ አመት ፍቃድ የሚሰጠው ቢሆንም የጠየቁት ፍቃድ ከተሰጣቸው በኋላ መነጠቃቸውን የገለፁት ዶ/ር ዳኛቸው፤ አቤቱታቸውን እስከ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ድረስ ለሚመለከታቸው ሁሉ ቢያቀርቡም ምላሽ እንደተነፈጋቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
“በአሜሪካ የሚገኙት ቤተሰቦቼ ስለናፈቁኝ እነሱን ሄጄ ማየት እፈልጋለሁ” ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ከዚህ በኋላ መብታቸውን ለማስከበር ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት መውሰድ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ “እድሜህ ስልሳ አመት ስለሞላና የጡረታ ሂደቱ በደንብ ተካትቶ ፋይልህ ውስጥ ስለሌለ የአመት ፍቃድህን ሠርዘነዋል” እንደተባሉ ገልፀው የነበረ ቢሆንም ከኮንትራት ውልና ከደሞዝ እግድ ጋር በተያያዘ ከዩኒቨርስቲው ጋር የነበራቸው ውዝግብ እልባት ማግኘቱን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው በኢህአዴግና በመንግስት አሰራር ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር የሚታወቁ ምሁር ቢሆኑም የማስተማር ሥራዬን ሳላቆም የየትኛውም ፓርቲ አባል መሆን አልፈልግም በሚል ራሳቸውን ከፓርቲ ፖለቲካ አግለው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

Addis Ababa

በቦረና ዞን ነዋሪ የሆኑት አቶ ጎንፋ አበራ ከፖሊስ በተተኮሰ 4 ጥይት ሕይወታቸው አለፈ

  •  


አስከሬኑ ሽኝት ላይ የነበሩ የአባያ ገላና ወረዳ ሰብሳቢ አቶ በድሉ መንግሥቱ በፖሊስ ተደብድው በእስር ላይ ናቸው

(ፍኖተ ነፃነት) በቦረና ዞን ገላና ወረዳ ቶሬ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጎንፋ አበራ ጳጉሜ 4 ቀን 2006 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ላይ ወታደር ዋቆ ሁቃ በተባለ ፖሊስ በተተኮሰ 4 ጥይት ህይወታቸው ማለፉን የቦረና ዞን የአንድነት አስተባባሪ አቶ ጌታቸው በቀለ ለፍኖተ ነፃነት ገለጹ፡፡ የአቶ ጎንፋ አስከሬን ወደ ቶሬ ከተማ ጤና ጣቢያ ተወስዶ ሐሙስ መስከረም 1 ቀን 2007 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ቤተሰባቸው ወደሚገኝበት አምቦ ከተማ ሲሸኝ የቶሬ ከተማ ነዋሪዎች አሸኛኘት ያደረጉ ሲሆን የአባያ ገላና ወረዳ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ በድሉ መንግሥቱ ከሽኝቱ ሲመለሱ በፖሊስ ተይዘው ድብደባ ከተፈጸመባቸው በኋላ በእስር ላይ መሆናቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ አቶ በድሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆናቸው ብቻ በተደጋጋሚ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ድብደባና እስር ይፈጸምባቸው የነበረና ባሳለፍነው ዓመትም ይሰሩበት የነበረ የግል ታክሲያቸውን በድንጋይ የሰባበሩባቸው ሲሆን አቶ በድሉና በአካባቢው ያሉ የፓርቲው አባሎች ግን እየደረሰባቸው ያለው ዛቻ፣ ማስፈራሪያና እስር ከትግሉ ፈቀቅ እንደማያደርጋቸው ሰላማዊ ትግሉንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡ ወደ ቶሬ ወረዳ ፖሊስ ደውለን ሁኔታውን ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡

Addis Ababa