ሥጋህ ይመዘናል
ለገበያ ይቀርባል
ደምህ ይወቀሳል
ዘርህ ይቆጠራል

የቆዳህ ቀለም
ወይ በር ያስከፍታል
ወይ ያዘጋብሃል
ኑሮን ስትታገል

ሲኖርህ ሰው ታፈራለህ
ስታጣ አስታዋሽ የለህ
ሲሳካ ፈላጊህ ብዛቱ
ስትከሽፍ ብቸኝነቱ

መኖርን ትኖራለህ
ተስፋ ሆኖ ምግብህ  
የሰውነትህ ዳገት
ቁልቁለቱ እስከ ሞት

እኔነትህ ተፈትጎ
ተበጥሮ ተወቅጦ
ተለስኖ ተመርጎ
ተወቅሮ ተለንቅጦ

ስቀህ
አልቅሰህ
ጠግበህ
ተርበህ

አፍቅረህ
ጠልተህ
ናፍቀህ
ረስተህ

ጉዞ ወደፊት…  

***